
—
የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ህዝብ ከመሠረታቸውና ካዳበራቸው ሁሉን አቀፍ የአስተዳደር ስርዓቶች መካከል ከፍተኛው ነው ማለት ይቻላል፡፡ የገዳ ሥርዓት የወንዶች የዕድሜ መደብ መሠረት አድርጎ የኦሮሞ ሕዝብ በመንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲ) ወግ የሚተዳደርበት ሥርዓተ ማህበር ነው። ገዳ አንድ ዓይነት ተቋማዊ ሥራ ብቻ የሚከናወንበት ሳይሆን፣ ፈርጀ ብዙና አያሌ ዘርፎችን በውስጡ ያካተተ፣ የኦሮሞን ሁለንተናዊ ሕይወት በሁሉም አቅጣጫ የሚመራ ሥርዓት ነው። በውስጡም የሚከተሉት ተቋማት ይገኛሉ።
ገዳ የተወሰነ ዑደት ያለው ሆኖ፣ በየስምንት ዓመቱ ከአንዱ የገዳ እርከን ወደሚቀጥለው እርከን የሚተላለፍበት እና ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገሩበት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። እያንዳንዱ የገዳ መደብለተወሰነ ጊዜ (ገዳ) በስልጣን ላይ የሚቆይበት ይህ ስርዓት በመደበኛ የስልጣን ማስተላለፍ ሥነ-ስርዓት የሚጀመርና የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ የገዳ ስርዓት የርስ በርስ ሚዛናዊ ክትትልና ቁጥጥርን፣ በየስምንት ዓመቱ በተከታታይ የሚደረግ የስልጣን ሽግግር፣ የስልጣን ክፍፍል (በአስፈፃሚ፣ በሕግ አውጭ እና በፍትህ አካላት)፣ ሚዛናዊ ተቀናቃኝ (በአምስት ፓርቲዎች መካከል) እና በከፍተኛ እና ዝቅተኛ መካከል የሥልጣን መጋራት መርሆዎች አሉት፡፡ የአስተዳደራዊ አካላት ስልጣን በአፋኞች እጅ እንዳይወድቅ ይከላከላል፡፡
እንደታዋቂው የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ታሪክ ጸሐፊ አስመሮም (1973) ገለጻ ገዳ የፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የአምልኮ ሥርዓቶችን በማካተት በየስምንት ዓመቱ እርስበርሳቸው በሚተካኩ የመደብ (ሉባ) ስርዓት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በየጊዜው የሚካሄዱ ምርጫዎች፣ ተጠያቂነት የሚሰፍንበት አሠራር፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚከናወንበት አካሄድ፣ ሀሳብን በነፃነት መግለፅ፣ እንዲሁም መግባባትን ታሳቢ ያደረጉ ረጃጅምና የተዋቀሩ ክርክሮች የማኅበረ-ባህላዊ ሃብቱን (የገዳ ስርዓትን) ዴሞክራሲያዊነት የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የስርዓቱ ገፅታዎች የኦሮሞ ህዝብን ውስጣዊ አንድነት ከማጠናከር ባለፈ የተለያዩ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች እና የፖለቲካ ፍላጎቶች ባሏቸው ህዝቦች መካከል የውይይት ባህልን በማጠናከር ሰላማዊ ግንኙነቶችን አዳብረዋል፡፡
ገዳ የኦሮሞን የዓለም አተያይ፣ ሥነምግባር፣ እሴቶችን እና ደንቦችን በመቅረፅ እንዲሁም የኦሮሞን ህዝብ እርስበእርስ እና ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በማስተሳሰር ረገድ ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በገዳ ስርዓት ውስጥ ያሉ ተቋማት ማህበራዊ ትስስርና ውህደት ለመፍጠር፣ የጋራመግባባት፣ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት፣ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር እንዲሁም ማህበራዊ መረጋጋት እና ዘላቂ የሀብት አያያዝን ለመፍጠር የታቀዱ ናቸው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀምባቸው የነበሩና አሁንም ግልጋሎት እየሰጡ ያሉ የበርካታ ግጭት ከልካይ ማኅበረ-ባህላዊ ሃብቶች ባለቤት ነው፡፡ የሥርዓቱ መርሆዎች የሁሉም ጎሳዎች፣ የዘር ሐረጎች፣ ክልሎች እና ኮንፌዴሬሽኖች ሚዛናዊ ውክልና፣ የመሪዎች ተጠያቂነት፣ በእርቀሰላም አለመግባባቶችን መፍታት እና መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች መከበራቸዉን ያካተቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም የገዳ ስርዓት ግጭትን ከመከላከል አንጻር የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡ ለምሣሌ “የገዳ ምክር ቤት ከአንድ ባህላዊ ክዋኔ በፊት ወይም በክዋኔው ወቅት የሚፈጠሩ ቀውሶችንና ማንኛውንም ዓይነት ግጭቶችን (ልማዳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊ፣ ህጋዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ) ይፈታል” በማለት አስመሮም በጽሁፉ ያብራረል (1973፡ 86)፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሃብቶች የኦሮሞን ህዝብ እርስበርስ ያጋመዱና ሰላማዊ መስተጋብርን ማጽናት የቻሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ከከሌሎች ወንድም ህዝቦችና ጎረቤቶቹ ጋር በሰላም አብሮ መኖር እንዲችል ማህበረ-ባህላዊ ምህዳሩን አመቻችቶለታል፡፡ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ማኅበረ-ባህላዊ ሃብቶች በግጭት ከልካይነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ በሚል የተጠቀሱ ናቸው፡፡
የገዳ እርከንና አኗኗር
የገዳ እርከን ማህበራዊ አገልግሎትንና ጠቀሜታን ማእከል በማድረግ የስራ ሀላፊነትና ተጠያቂነትን ለህዝቦች በመስጠት የተዋቀረ ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ ይመሰረታል፡፡ ይህም አንደኛው አባቶቻቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑት እንደ ተወለዱ የመጀመሪያው ገዳ እርከን ይገባሉ፡፡ ይህም ማለት አባቱ ስልጣን ላይ እያሉ የተወለደ ልጅ ዳባሌ ይገባል፡፡ ይህ ከ40 አመት በኋላ አባ ገዳ የመሆን እድል ያለው ይሆናል፡፡ ሌላው የጃርሳ ልጆች በትውልድ እድሜ እኩል ሳይሆኑ በአንድ ገዳ እርከን ውስጥ የሚገኝ ማለት ነው፡፡ ይህም አባቶቻቸው ከገዳ የወጡ ልጆች ማለት ነው ወይንም፡፡ ይህም እንተወለዱ የሚገቡት እርከናቸው ደግሞ ሌላ እርከን ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ40 አመት ቀድመው ገዳ ይገባሉ ወይንም ዘግይተው ከገዳ ይወጣሉ በዚህ ምክንያት አባ ገዳ የመሆን እድል ሊያጡ ይችላሉ፡፡ የማህበራዊና የስራ ድርሻ እንደየእድሜ ያቸው ተመሣሣይ ሲሆን የስላጣን ተጠያቂነታቸው ላይ ልዩነት ይኖራቸዋል፡፡ በአጠቃለላይ ስም የእርከን ስሞች እንደሚታወቀው ይከተላሉ፡
1. ደበሌ ከ0—8
2. ጋሜ ከ9-16
3. ፎሌ ከ17-24
4. ራባ ከ25-32
5. ዶሪ ከ33-40
6. ገዳ ከ41-48
7. ዩባ 1 ከ49-56
8. ዩባ 2 ከ57-64
9. ዩባ 3 ከ65-72
10. ዩባ 4 ከ73-80
11. ገዳሞጂ ከ80 በላይ
ማንኛውም የኦሮሞ ወንድ ከተወለደበት ዕለት ጀምሮ በገዳ ሥርዓት ይታቀፋል። ሲታቀፍም ከገዳ መደቦች መካከል የአንዱ አባል በመሆኑ ነው። በጥንቱ የገዳ ሥርዓት የገዳ መደቦች ብዛት ዐሥር ሲሆን፣ ከዐሥሩ የገዳ መደቦች መካከል የመጀመሪያዎቹ አምስት መደቦች የአባቶች ሲሆኑ፣ ቀጣዮቹ የገዳ መደቦች ደግሞ የልጆች ገዳዎች ናቸው። አምስቱ የገዳ መደቦች ዑደት (አንዳንዴ ቡታ ይባላሉ)። እያንዳንዳቸው መጠሪያ ስሞች አሏቸው።
ገዳ ወይንም ገዶማ ከሁሉ እርከኖች እጅግ በጣም ወሳኝ እርከን ነው፡፡ ይህም የፖለቲካና ማህበራነት መሪነትን የሚጨብጡበት ስልጣን ብቻ ሳይሆን የሀገር እጣፈንታ በእጅ ላይ የሚወድቃበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ እርከን በጣም ወሣኝና እጅግ አስፈላጊ እርከን ሲሆን የገዳ ትልቁ ስልጣን የሚይዝበት እንዲሁም የእምነት መሪነትም የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ አባ ገዳ በገዳ ሥርዓት ሕግ ለስምንት ዓመታት ብቻ እንዲያገለግሉ በሕዝብ ተመርጠው ሥልጣን ላይ የሚወጡ ባለሥልጣኖች ወይም የአስተዳደር አብላጫ ቁንጮ ነው።
እያንዳንዱ የገዳ ሥልጣን ዘመን 8 ዓመት ነው። ሥልጣን ላይ የሚቆዩ 5 ገዳዎች አሉ። ስለዚህም የገዳ የሥልጣን ዑደት 40 ዓመት ይሆናል። በሌላ አገላለጽ በ40 ዓመት ዑደት ውስጥ 5 ገዳዎች አሉ ማለት ነው። አንድ ሰው አሁን ሥልጣን ቢይዝ ወይም ሉባ ቢሆን ከዛሬ 40 ዓመት በኋላ ደግሞ የሱ ልጅ ሉባ ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም ገዳ ዐውደ ግዛት ይሰኛል።
መጽሐፉን በ PDF ለማንበብ የምትፈልጉ ካላችሁ ከሥር የሚገኘውን Link በመጫን ማውረድ ትችላላችሁ።