
ፊንፊኔ፣ መስከረም 14 ቀን 2019 ዓ.ም — የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ አውጥቶ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ለዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የብልፅግና ፓርቲ መንግሥት ለእውነተኛ እርቅ በር እንዲከፍት በአጽኖት ጠይቋል።
የጦርነቱ አስከፊ ውጤት
መግለጫው እንደሚያስረዳው፣ በኦሮሚያ ውስጥ ለዓመታት ሲካሄድ የቆየውና አሁንም እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማምጣቱ የማይካድ እውነት ነው። በዚህ ጦርነት የብዙ ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የብዙ ንጹሃን ዜጎች ደም ፈሷል።
የሕዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ የነበረበት ነገር ግን በዚህ ጦርነት ምክንያት የተደመሰሰ እና የባከና የሀገራችንና የሕዝባችን ሀብት ቢሰላ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።
የተሳሳተ የጦርነት ውሳኔ
ኦነግ እንዳስታወቀው፣ ባለው የኃይልና የኢኮኖሚ አቅም በመተማመን፣ ለእውነተኛ እርቅና ለጋራ መግባባት እራስን ባለማዘጋጀት የጦርነት ውሳኔ መወሰዱ ምን ያህል ጥፋት እንዳስከተለ ለሁሉም ሰው ግልፅ ነው። በዚህ ጦርነት የተገኘ ውጤት ቢኖር የሕዝባችንን መከራ ማባባስ፣ ሕይወቱንና ኑሮውን ማናጋት እና ሰላም እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ ለነባሩ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ እንዳላመጣ ኦነግ ያምናል።
ለእውነተኛ እርቅ ጥሪ
በኦሮሚያ ውስጥ የብዙ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለመፍታት፣ እውነተኛና ፍትሃዊ የሆነ እርቅ በመታጣቱ ጦርነቱ መልክ እየቀየረ እንዲቀጥል አድርጎታል። ስለሆነም የብልፅግና ፓርቲ መንግሥት (PP) በኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ላለው ጦርነት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሲባል ለእውነተኛ እርቅ በር እንዲከፍት ኦነግ በአጽኖት ይጠይቃል።
የኦሮሞ ትግል እና የብሔሮች መብት
የኦሮሞ ብሔራዊ ነፃነት ትግል የኦሮሞን መብትና ነፃነት ለማስመለስ የሚካሄድ ነው። የኦሮሞ ሕዝብም መብቱና የሀገር ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ይታገላል። የኦሮሞ ሕዝብና ትግሉ የብሔሮችን መብት ሙሉ በሙሉ የሚያከብሩ ናቸው።
የሰሜን ጥምረት አደጋ
ኦነግ እንዳስጠነቀቀው፣ የሰሜን ጥምረት አካሄድና ዓላማው ኦሮሚያን የጦር አውድማ ማድረግ፣ በሕዝባችን ላይ የከፋ ጥፋትና መከራ ማምጣት፣ እስካሁን የተጎናፀፍናቸውን መብቶች ማሸርሸር፣ ኦሮሚያን እንደገና መያዝ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መዝረፍ፣ እንዲሁም በምድራችንና በሕዝባችን ላይ ያልተፈለገና ያልተጠበቀ አደጋ ለማምጣት መሆኑ ታዉቆ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ ብሔሮችን መብት እያከበረና እየጠበቀ፣ ያለ ምንም የፖለቲካ ልዩነት ቄውንና ወሰኑን አጥብቆ እንዲጠብቅ ኦነግ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።
የአንድነት ጥሪ
አሁን ያለንበት ወቅት በዝምታ የምናልፍበት ስላልሆነ፣ የኦሮሚያ መንግሥት ሁሉም የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ጥላ ሥር ተሰባስበው የኦሮሞን ጥቅም ሳይሸራርፉ እንዲጠብቁ ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ኦነግ ቀደም ብሎ ያቀረበውን ጥሪ በድጋሚ ያድሳል።
የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ
ጦርነት መፍትሔ እንደማያመጣ ሁሉ፣ ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከታቸውና በፓርቲ ደጋፊነታቸው ምክንያት ወንጀለኛ ማድረግና ማሰር መፍትሔ የሚያመጣ ስላልሆነ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መንግሥትን በድጋሚ እናሳስባለን።
ለኦሮሞ ጥቅም እንታገላለን እያሉ…
ለኦሮሞ ጥቅም እንታገላለን እያሉ የጠላት በትር በመሆን፣ ሕዝባችን በከባድ መስዋዕትነት ያስወገደውን የጨቋኝና የብዝበዛ ሥርዓት በሕዝባችን ላይ በአዲስ መልክ መልሰው ወደ ኦሮሚያ የሚስቡ አካላት ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ በማወቅ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ አስጸያፊና አሳፋሪ አካሄድ እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ኦነግ አጥብቆ ያሳውቃል።
የመጨረሻ ጥሪ
በመጨረሻም፣ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕዝባችን ወደ ሰላምና መረጋጋት ምዕራፍ እንዲሸጋገር እንዲሁም ያሉት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ፣ ለእርቅና ለሁሉ አቀፍ ውይይት ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የሚዲያ አንቀሳቃሾች አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርጉ፣ ሕዝባችንም ይህንን ሃላፊነት በራሱ ተነሳሽነት ተረክቦ ለማሳካት እንዲሰራ ኦነግ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለሰፊው ሕዝብ!
ምንጭ፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)

