
ኦቦ ሌንጮ ለታ
በበርካቶች ዘንድ በፖለቲካ ሰውነታቸው በጉልህ ይታወሳሉ። ገና በለጋ ዕድሜያቸው የጀመሩት በትጥቅ የተደገፈው የፖለቲካ ትግላቸው በበርካታ ውጣ ውረዶች የተሞላ እንደሆነ ታሪካቸው ይመሰክራል።
ትውልዳቸውና እድገታቸው ወለጋ ደምቢዶሎ ነው።ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉት ደግሞ አዳማ።ወደአሜሪካ አቅንተው ከፍተኛ ትምህርታቸውን በኬሚካል ኢኒጂነሪንግ ተመርቀዋል። በቅርብ የሚውቋቸው ሁሉ አንባቢ እና ፈጣን አእምሮ ያላቸው ናቸው ይሏቸዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) ከመሰረቱት ቀዳሚ አመራሮች አንዱ ናቸው። በትጥቅ የታገዘው የትግል ታሪካቸው ከሀገር ውስጥ እስከውጪ የሚታወቁበትም ሆኖ አልፏል። አብዛኛውን እድሜያቸው በትግል ነው ያሳለፉት።«ሶስት ልጆች ወልጃለው።ልጆቼን ወለድኳቸው እንጂ አላሳደኳቸውም።እኔ ዘመኔን ሁሉ ታጋይ ሆኜ ተለይቻቸው ነው የኖርኩት።ባለቤቴም በደርግ ለ10 ዓመት ታስራ ስለነበር ልጆቻችን ተገቢውን የወላጅ ክብካቤ አላገኙም ነበር »ሲሉ ይናገራሉ።
በወጣትነት ስህተት መስራታቸውን በትጥቅ ትግል እና በአብዮት መንግስት መጣል ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር እንደማያስችል ዘግይተው መረዳታቸውን በዚህ ምክንያት የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴን መደገፍ ማቆማቸውን ይገልጻሉ።በምትኩ ወደዲሞክራሲ የሚወስዱ የሲቪልና የፖለቲካ ጥረቶችን መደገፍ ምርጫቸው መሆኑን ያወሳሉ።
አሁን ድረስ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ በመሆን ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ በማዋጣት የሚታወቁት ኦቦ ሌንጮ፤ በሚሰጧቸው አስተያየቶች በአንዳንዶች ዘንድ አወዛጋቢ ቢባሉም ለአገር ይጠቅማል የሚሉትን ከማዋጣት ወደሗላ እንደማይሉ ይናገራሉ።
ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ “ለተሻለ ነገ እናንብብ” በሚል በጀመረው የመቶ ቀናት ግድድር፤ ኦቦ ሌንጮ ለታም የምንጊዜም ምርጦቼ ናቸው ያሏቸውን መፅሐፍት እንደሚከተለው አሳውቀውናል።
1- War and Peace በሊዮ ቶሎስቶይ
2- Nineteen Eighty – Four በጆርጅ ኦርዌል
3- The Wretched of the Earth በፍራንቴዝ ፋኖን