የግጭቶች መቆምና የፀጥታ ዋስትና

በኢትዮጵያ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ስለመፍጠር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰጠ ጋዜጣዊ የጋራ መግለጫ

*************

ቀን መቁጠሪያ ዴሞክራሲ አይደለም፤ ለ2018 ዓ.ም ምርጫ የተጀመረውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የምርጫ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት መሰረታዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በጋራ እንጠይቃለን።

እኛ ስማችን ከሥር የተዘረዘረው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ2018 ዓ.ም.ጠቅላላ ምርጫ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተልን ነው፡፡ ይህንን የአሰራር ሂደት ከቦርዱ ተግባርና ኃላፊነት አንጻር የምንገነዘብ ቢሆንም፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት የዴሞክራሲያዊ ሂደት መሰረት በሌለበት ሁኔታ፤ በተጀመረው እንቅስቃሴ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው ባልተረጋገጠበት ጥረቱ ሁሉ ትርጉም አልባ መሆኑን በግልፅ መናገር እንፈልጋለን።

ቀደምት የኢትዮጵያ ምርጫዎች አግላይ፣ ጠቅላይና አምባገነናዊ ለሆነ የፖለቲካ ስርዓት ህጋዊነትን ለማላበስ የሚደረጉ የፖለቲካ ትወናዎች ሆነው ቆይተዋል። እነዚህ ያለፉት ምርጫዎች በሂደታቸው ነፃ፣ፍትሃዊና አሳታፊ፣ በውጤታቸውም ተኣማኒና በህዝብ ተቀባይነት ያገኙ አልነበሩም።

በዚህም ምክንያት የሀገሪቱን ጥልቅ የፖለቲካ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ የግጭትና ያለመረጋጋት አዙሪትን ሲያባብሱ ቆይተዋል። እውነታው ምርጫ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት መገለጫ እንጂ የገዢዎች ሥልጣን ማስረገጫ ሊሆን አይገባም:: ስለሆነም የ2018 ዓ.ም. ምርጫ ካለፈው ታሪክ የተለየና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት የሚያስችል እውነተኛ እርምጃ እንዲሆን፤ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አማራጭ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አበክረን እናሳስባለን ፡፡

ስለሆነም ሀገራችን ስለምርጫ ፍኖተ ካርታው/ ሂደቱም ሆነ የጊዜ ሰሌዳው ትርጉም ባለው ደረጃ ከመወያየቷ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሚከተሉት የማይታለፉ መሰረታዊ ሁኔታዎች ላይ አፋጣኝና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ እናቀርባለን። እኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ በጋራና በተናጠል ስናሳስብ ቆይተናል። በመሆኑም አሁንም ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድ ወሳኝ ናቸው የምንላቸው የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

1. ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር

መንግስት ከሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በእውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር የጋራ ፍኖተ-ካርታ ላይ ለመስማማት የሚያስችል አፋጣኝና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት መጀመር አለበት። ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በስደትና በትጥቅ ትግል የሚገኙትን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና ባለድርሻ አካላት መካከል ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና ዕርቅ ማውረድ አስፈላጊ ነው። በሀገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ድርድር ሳይደረግና ስምምነት ላይ ሳይደረስ የሚካሄድ ምርጫ የፖለቲካ ቀውሱን ከማባባስ ውጪ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልምና በድርድር ስምምነት ላይ ሊደረስ ይገባል።

2. የግጭቶች መቆምና የፀጥታ ዋስትና

መንግሥት የሀገሪቱን ሠላና ጸጥታ የማረጋገጥ ቀዳሚና ዋነኛ ተግባርና ኃላፊነቱ ቢሆንም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣በትግራይ፣ በአፋርና በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ አውዳሚ ጦርነቶችና ግጭቶች እየተሰፋፉና እየከፉ ነው፡፡ ይህ እውነታ በአፋጣኝ፣ በቋሚነትና በሚረጋገጥ መልኩ መቆም አለበት። ሰላምና ፀጥታ ለማንኛውም አስተማማኝ ምርጫ መሰረት ሲሆኑ፣ ፓርቲዎችና እጩዎቻቸው፣ መራጮች፣ ገለልተኛ ታዛቢዎችና የዲሞክራሲ ተቋማት/ መገናኛ ብዙሃን በመላ ሀገሪቱ በነፃነትና በደህንነት መንቀሳቀስ ለምርጫው ተኣማኒነት፣ ተቀባይነትና ዲሞክራሲያዊነት ወሳኝ ናቸው።

3. የፖለቲካ ምህዳሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መከፈት

መንግስት አሁንም በግፍ ታስረው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ መልቀቅ አለበት። በህገ-ወጥ መንገድ በመላ ሀገሪቱ የተዘጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲ ቢሮዎች እንዲከፈቱ መደረግና በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰው ማዋከብና ማስፈራራት ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ የፓርቲ አመራሮችና አባላት በእስር ላይ በሚገኙበትና ቢሮዎቻቸው በተዘጉበት ሁኔታ በምርጫ መሳተፍ እጅግ ፈታኝ ብቻ ሳይሆን ከአጃቢነት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውምና መስተካከል እንዳለበት ይታመናል።

4. መሰረታዊ የዲሞክራሲ የተቋማትና የህግ ማሻሻያዎች

የህዝብን እምነት ለመመለስ ቁልፍ የዴሞክራሲ ተቋማት ከተጽዕኖ ነጻ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው። እኛ ከነዚህ ዋናውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ- ምርጫን የማስፈጸም አቅምና ብቃት አለውን ? የሚለውን ጥያቄ አስቀድመን፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውክልናና ተሳትፎ፣ በግልፅና በስምምነት ላይ በተመሰረተ ሂደት፣ ከላይ/ከቦርዱ እስከ ታቺኛው/ምርጫ ጣቢያ በነጻና ገለልተኛ ብቁ አባላት እንደገና እንዲዋቀር እንጠይቃለን። በተጨማሪም የምርጫ ህጉ ሁሉን አቀፍ፣ ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ውክልናን የሚያረጋግጥ ስርዓት ለመፍጠር መሰረታዊ ማሻሻያ ሊደረግበት፣ እና የፓርቲዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ድንጋጌ ከህጉ ሊወጣ ይገባል።

5. የመንግስት መዋቅሮች ገለልተኝነት ማረጋገጥ

በእኛ እምነት ገለልተኛና ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ የጸጥታ መዋቅር መፍጠር ለምርጫ ወሳኝ ነው። የጸጥታ ሃይሎች የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያከብሩና ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። ዜጎች ያለስጋት በሰላም ተንቀሳቅሰው ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉበት አስተማማኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። በመሆኑም የፀጥታ ሀይሎች—የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም የደህንነት ተቋማትን—እንዲሁም የፍትህ አካላትን ሙሉና ተጨባጭ ገለልተኝነት የሚያረጋግጥ በህግ የሚያስገድድ የጋራ ስምምነት መኖር አለበት። እነዚህ ተቋማት ገዥውን ፓርቲ ሳይሆን ሐገርንና ህገ-መንግስቱን ማገልገል አለባቸው።

6. የፕሬስ ነፃነትን ማረጋገጥ

በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ስደት መቆምና ገለልተኛ ሚዲያዎችን የሚያፍኑ ህጋዊና አስተዳደራዊ እንቅፋቶችን ማስወገድ ለአንድ ግልፅ የምርጫ ሂደት ወሳኝ ነው። ስለሆነም ለሁሉም የአገር ውስጥና የውጪ/ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ምርጫ ጣቢያዎችና መረጃዎች እኩል ተደራሽነት እንዲኖራቸውና የማሰራጨት ገደብ እንዳያጋጥማቸው ይደረግ ዘንድ ይጠበቃል፡፡

7. የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ተሳትፎ

መንግስት ምርጫው ፍትሃዊ፤ አሳታፊና ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ የሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና የሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት በምርጫ ሂደቱ ከቅድመ ምርጫ የአስቻይ ሁኔታዎችና የምርጫ ምዝገባና ዝግጅት ዳሰሳ ጥናት እስከ ድኅረ-ምርጫ ኩነቶች ክትትል፣ ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው ስለመሳተፋቸው በግልጽ መደንገግና ለተግባራዊነቱም ተገቢና አስፈላጊ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ምርጫ ቦርድ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች የሚባሉት ነጻነታቸውና ገለልተኝነታቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይረጋገጥ መመደብ የምርጫውን ተኣማኒነትና ተቀባይነት አያረጋግጥምና ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

እነዚህ ተስፋዎች ባዶ ቃላት እንዳይሆኑና የፍትሃዊ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች መሟላት በአፍሪካ ህብረት (AU)፣በአውሮፓ ህብረት (EU) እና፣ በተባበሩት መንግስታት (UN) በሚገኙ ገለልተኛ አለም አቀፍ ተዋናዮች ክትትል ሊደረግባቸውና በዋና ዋና የምርጫው ተሳታፊዎች – በምርጫ ቦርድ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የዲሞክራሲ ተቋማት መካከል አስተማማኝ መተማመንና ስምምነት መደረስ በይፋ ሊረጋገጥ ይገባል።

ስለሆነም እኛ የመግለጫው ባለቤቶች መንግስትና ገዥው ፓርቲ እነዚህን መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲያሟሉና ለሁሉም ወገኖች ነፃና ፍትሃዊ የሆነ የውድድር ምህዳር እንዲፈጥሩ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን ። እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የሚደረግ ማንኛውም ምርጫ የህዝብን ፍላጎት ከመግለጽ ይልቅ የይስሙላ ዲሞክራሲ ማሳያ እንደሚሆን እናምናለን።

እኛ ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ አንድ ፓርቲ ብቻውን ቀርቶ የተወሰኑ የዲሞክራሲ ተቋማት ብቻቸውን ሊወጡት የማይችሉት ታላቅ ተግባር ነው ብለን በፅኑ እናምናለን ፡፡

ስለሆነም እኛ የዚህ መግለጫ ባለቤት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፡-

– በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ሃቀኛ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ሀይሎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣…ሁላችንም ባለድርሻ አካላት በአንድነት እንድንቆም ጥብቅና አስቸኳይ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

– በሀገር ዘላቂ ሠላምና ልማት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በህዝብ መተሳሰብና መረዳዳት፣ አብሮነትና ፍቅር ያለተቀናቃኝነት በአጋርነት በመቆም እነዚህን መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች በጋራ እንጠይቅ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

– የ2018 ዓ.ም. ምርጫ ታሪካዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፣ መጀመሪያ መገንባት ያለበትን የዴሞክራሲ መሰረት ከገነባን ብቻ ነውና በአንድነት የመቆማችን ተልዕኮ ለነገ የሚባል አይደለምና እንተባበር ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

– የኢትዮጵያችን ወዳጅ ሀገራትና አጋር ዓለማቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ህዝቦች ለሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በምናደርገው ትግል ከጎናችን በመቆም ለሀገራችንና ህዝቦቿ ከፍተኛ ውለታ እንድትውሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አንድነት ኃይል ነው!! የተባበረ ትግል ያሸንፋል!!

የተቃዋሚ ፓርቲዎች :-

1) ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ)

2) የመላው ሲዳማ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ (መሲሕዴአፓ)

3) ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)

4) የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)

5) የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)

6) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት መድረክ (መድረክ)

7) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)

8 ) የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ)

9) የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን)

10) ዐረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዐረና ትግራይ)

አዲስ አበባ፣

ህዳር 03, 2018 ዓ.ም.

Leave a comment